የምዕራባውያንን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫናና ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የፊታችን እሑድ በዋሺንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው፡፡
ሰልፉ በኋይት ሃውስ ፊት ለፊት በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ ሦስት ሰአት ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የባይደን አስተዳደር በአሸባሪው ሕወሓት ላይ የያዘውን የተለሳለሰ አቋም እና በኢትዮጵያ ላይ እያደረገ ያለውን ጫና የሚቃወሙ መልዕክቶች እንደሚተላለፉ የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዋሺንግተን ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡
የምዕራባውያን ሀገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚያስተላልፉትን የተሳሳተ መልዕክት የሚቃወሙ መልዕክቶች እንደሚተላለፉ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች መንግስት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሰላምን ለማስፈን እየወሰደ ያለውን እርምጃ ድጋፋቸውን የሚገልጹበትና ለኢትዮጵያ ያላቸውን አጋርነት የሚያሳዩበት ነው ብለዋል።
እንዲሁም ህዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች “ለሀገራዊ ጥሪ ወገናዊ ምላሽ” በሚል መሪ ሀሳብ የገቢ ማሰባሳቢያ መርሐግብር በዋሺንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡