ሀገራችን ለትጋታችን በምላሹ የለምነቷን ፍሬ እንደምታጠግበን አይተናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራችን ኢትዮጵያ ለትጋታችን በምላሹ የለምነቷን ፍሬ እንደምታጠግበን አይተናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅማ ዞን ሸቤ ሶምቦ ወረዳ በሩዝ የለማ ማሳን ጎብኝተዋል።
በጅማ ዞን፣ በሦስት ወረዳዎች ላይ ከተንሰራፋው የኪሼ ኩታ ገጠም የሩዝ ልማት፣ በሸቤ ሶኖ ወረዳ በኩል የሚገኘውን የሩዝ ምርት ማየታቸውንም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አክለውም ፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለትጋታችን በምላሹ የለምነቷን ፍሬ እንደምታጠግበን ያየንበት ነውም ብለዋል።
በተጨማሪም በጅማ ከተማ በ10 ሄክታር ላይ ያረፈ ጥምር ግብርናን መጎብኘታቸውን አንስተው ፥ በወጣት ትኩስ ጉልበት፣ መሬትን በውጤታማነት መጠቀምን በተገበረ ሁኔታ አትክልትና ፍራፍሬን ያመርታልም ነው ያሉት፡፡
በዚህም የአሣ እርባታን ይከውናል፣ የንብ ማነቢያንም አካትቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጠንክረው ሠርተው ለሌሎችም የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ወጣቶች ለሀገር ኩራት እና ለብዙዎች አርዓያ እንደሚሆኑም ነው ያሰፈሩት።
በያለንበት ዘርፍ በርትተን እንትጋ ሲሉም ጥያቄ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዞኑ በዚህ ዓመት ከ27 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ ተሸፍኗል ።
በ2013/2014 የምርት ዘመን በዞኑ ሩዝ ተዘርቶ የነበረው ከ2 ሺህ ሄክታር በማይበልጥ መሬት ላይ ነበር።
በዚህ አመት ስራው በመስፋፋቱ ከጅማ ዞን ብቻ ከ1 ሚሊየን ኩንታል በላይ የሩዝ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
አርሶ አደሮች ሩዝን በኩታ ገጠም ነው የዘሩት ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በጎበኙት ሸቤ ሶምቦ ወረዳ ኪሼ ክላስተር 3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ማሳ በሩዝ ለምቷል።
የሩዝ ምርቱ ከተነሳ በኋላ ስንዴ ለመዝራት መዘጋጀታቸውንም አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል ።
በአልዓዛር ታደለ