Fana: At a Speed of Life!

በሕገ-ወጥ መንገድ ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ሲያንቀሳቅስ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገ-ወጥ መንገድ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ሲያንቀሳቅስ የነበረ ግለሰብ ከ25 ግብረ-አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገባቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኅብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማና ባደረገው ብርቱ ክትትል ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡

በወንጀሉ የተጠረጠረው ሳሙኤል እጓለ አለሙ በቅፅል ስሙ ሳሚ ዶላር የሚባል ሲሆን፥ ነዋሪነቱን በአዲስ አበባ ከተማ በማድረግ ወደ አሜሪካ ሀገር በተደጋጋሚ የሚመላለስ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ግለሰቡ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች፣ የቤት እና የቢሮ እቃዎች እንዲሁም ተዛማጅ መገልገያዎች የችርቻሮ ንግድ ፍቃድን ሽፋን በማድረግ ሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬና በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ተጠርጥሮ በራሱና ዮዲት እጓለ አለሙ ከተባለች እህቱ ጋር በመሆን በስማቸው በተለያዩ ባንኮች በከፈቷቸው 25 የባንክ አካውንቶች በአንድ ዓመት ውስጥ ከ247 ሚሊየን ብር በላይ ማንቀሳቀሳቸውን ፖሊስ ደርሶባቸው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ግለሰቡ ከ25 የወንጀል ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን በህገ-ወጥ መንገድ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ሲያንቀሳቅሱ እንደነበር በቅድመ ምርመራ እንደተደረሰበት ተጠቁሟል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በሕገ-ወጥ የውጭ ሀገር የገንዘብ ዝውውር፣ በግብር ስወራ ወንጀል እና ከህወሓት የሽብር ቡድን ጋር የግንኙነት መረብ በመፍጠር ከፍተኛ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ እንደነበር ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው ተብሏል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በአጠቃላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ5 ቢሊየን 248 ሚሊየን ብር በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያንቀሳቅሱ እንደነበር ፖሊስ ባደረገው ምርመራ የደረሰባቸው መሆኑንም የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ኅብረተሰቡ ላደረገው ቀና ትብብር ፖሊስ ምስጋና አቅርቧል፡፡

ዜጎች ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ሲመለከቱም በአፋጣኝ በስልክ ቁጥሮች 0115 30 91 39፣ 0111 11 94 75፣ 0111 71 10 12 እንዲሁም 816 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.