በጋምቤላ ከተማ በትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ከተማ ባሮ ማዶ አካባቢ በተከሰተ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡
የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ኡቻን ኡቦንግ እንደገለፁት÷ በአደጋው ሦስት ልዩ ኃይል ፖሊሶችን ጨምሮ አንድ የጥበቃ ሠራተኛ ሕይወት አልፏል፡፡
አሽከርካሪውን ጨምሮ በሥድስት ሰዎች ላይ ደግሞ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡
አደጋው የተከሰተው ትናንት ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ ልዩ ኃይል ፖሊሶችን ጭኖ ለሥራ ሲንቀሳቀስ የነበረ ተሽከርካሪ መንገድ ጥሶ በመውጣቱ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አደጋው ከደረሰባቸው ሰዎች በተጨማሪ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት መረጃ ያመላክታል፡፡
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡