Fana: At a Speed of Life!

ክልላዊ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ማስጀመሪያ መርሃግብር በሀላባ ዞን እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል የ2015 በጀት ዓመት የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ማስጀመሪያ መርሃግብር በሀላባ ዞን ዌራ ዲጆ ወረዳ እየተካሄደ ነው።

የዘንድሮው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ “የተፈጥሮ ሃብታችን ለሁለንተናዊ ብልጽግናችን”በሚል መሪ ቃል ለአንድ ወር እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

ሥራውን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት እንዲሰራም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በክልላዊ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች እንዲሁም ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

አቶ ርስቱ ይርዳ መርሃ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት ፥ ክልሉ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የመሬት መራቆት የሚታይበት ነው።

በአካባቢ መራቆት ምክንያት የጎርፍ አደጋ ፣የመሬት መንሸራተትና መሰል ችግሮች መስተዋላቸውን የተናገሩት አቶ ርስቱ ፥ ችግሮቹን ለመፍታት የአካባቢ እንክብካቤና ጥበቃ ስራን በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል።

የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራን በላቀ ደረጃ መፈጸም የህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተውም ፥ የለማ አካባቢን መፍጠር ካልተቻለ የምንመኘውን ብልጽግና ማረጋገጥ አዳጋች ነው ብለዋል።

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተፋሰስ ልማት ስራን ማከናወን አብይ ጉዳያችን አድርገን መስራት ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።

በኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤሊያስ እንደገለጹት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ 6 ነጥብ 9 ሚሊየን ህዝብ ርዳታ ጠባቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓመት እስከ 1ቢሊየን ዶላር የእርዳታ እህል ግዢ ለመፈጸም እንደሚዉልም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያብራሩት።

በዘርፉ የሚያጋጥመውን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄ/ር በላይ መሬት የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ለማከናወን መታቀዱንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት ፥ በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫችን ነው።

ባለፈው ዓመት ከ3ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ከ2መቶ 73ሺ 400 ሄ/ር በላይ መሬት የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን ማከናወን መቻሉንም ነው የጠቆሙት።

ዘንድሮ ከ753 ሺ ሄ/ር በላይ መሬት የሚሸፍኑ ከ3ሺ 100 በላይ የማህበረሰብ ተፋሰሶች ውስጥ ከ293ሺ 400 ሄ/ር መሬት በላይ ለማልማት ግብ መጣሉን አቶ ኡስማን ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.