በአማራ ክልል ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ከፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ተባብሮ በመስራት የሽብር ተግባር ፈፅሟል በሚል ተጠርጥሮ ሲፈለግ የነበረው ጎበዜ ሲሳይ በቁጥጥር ስር ዋለ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ከፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ተባብሮ በመስራት የሽብር ተግባር ፈፅሟል በሚል ሲፈለግ የነበረው ጎበዜ ሲሳይ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
ግብረ ኃይሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ÷ ግለሰቡ አምልጦ ጅቡቲ ከገባ በኋላ ወደሌላ አገር ሊሻገር ሲል ከዓለም አቀፉ ፖሊስ እና ከጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር እንዲውልና ተላልፎ ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ተደርጓል ብሏል፡፡
ዛሬ ምሽትም አዲስ አበባ መግባቱን ነው ግብረ ኃይሉ ያስታወቀው፡፡
በአማራ ክልል ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ክልላዊ ስልጣንን በኃይል ለመያዝ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በህቡዕ ተደራጅተውና ተቀናጅተው በሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ግብረ ኃይሉ ሚያዝያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።
በዚህ መሰረትም ፦
1. ሀብታሙ አያሌው፣
2. ምንአላቸው ስማቸው
3. ብሩክ ይባስ እና
4. እየሩሳሌም ተ/ፃዲቅ
5. ዘመድኩን በቀለ
6. ልደቱ አያሌው
7. መሳይ መኮንን
8. ጎበዜ ሲሳይ
9. ምህረት ወዳጆ (ምሬ ወዳጆ)
10. በለጠ ጋሻው እና
11. ሙሉጌታ አንበርብር የተባሉት ተጠርጣሪዎች በፈፀሙት የሽብር ተግባር እንደሚፈለጉና ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት ኢንተርፖል ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንደሚቀርቡ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ማሳወቁ ይታወሳል።
ከነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል ጎበዜ ሲሳይ ዘገየ በአማራ ክልል ቆቦ አካባቢ የጽንፈኛ ታጣቂ ኃይሎችን በማደራጀት፣ በቅርቡም በጽንፈኞች ግድያ የተፈጸመበትን ግርማ የሺጥላን ግድያ በማስተባበር ሚና እንደነበረው ነው የተገለጸው፡፡
እንዲሁም በመከላከያና በህዝቡ ላይ ጽንፈኞች ጥቃት እንዲያደርሱ በማደራጀትና ቃል አቀባይ ሆኖ በማስተባበር የሽብር ተግባር ውስጥ በመሳተፍ ተጠርጣሪ በመሆን ሲፈለግ መቆየቱም ተገልጿል፡፡
ግለሰቡ አማራ ክልልን በማሸበርና ስልጣንን በኃይል በመቀማት በቀጣይም የፌዴራል መንግስትን ለማፍረስ ሲንቀሳቀስ ከነበረ ጽንፈኛ አካል ጋር በመተባበር ሲሰራ እንደነበር በመጠርጠሩ÷ ግለሰቡን ጨምሮ ሌሎች በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የጋራ ግብረ ኃይሉ ከኢንተርፖል ጋር ባለ ስምምነት መሰረት ሲሰራ መቆየቱን ገልፆ ነበር።
በዚሁ መሰረትም አስፈላጊውን ፎርማሊቲና አግባብ ያላቸው መረጃዎችን በማደራጀት ጎበዜ ሲሳይ አምልጦ ጅቡቲ ከገባ በኋላ ወደሌላ አገር ሊሻገር ሲል ከዓለም አቀፉ ፖሊስ እና ከጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር እንዲውልና ተላልፎ ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ተደርጎ ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ገብቷል ነው ያለው ግብረ ኃይሉ።
የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አሁንም ኢትዮጵያ ባለት ስምምነት መሰረት ሌሎች ያልተያዙ የሽብር ቡድኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰራ መሆኑን ገልጿል።