ጀርመን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የጀርመን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ዋና ዳይሬክተር ቢርጊት ፒከል ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ቦርድ ስብሰባ ጎን ለጎን የተካሄደ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
አቶ አህመድ ሽዴ ጀርመን በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ለምታደርገው የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እና ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የጀርመን ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ቢርጊት ፒከል በበኩላቸው÷ ጀርመን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ስራ ለመደገፍም ጀርመን ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በተመረጡ ዘርፎች በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡