Fana: At a Speed of Life!

በኦጋዴን ተፋሰስ የለማ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችትን ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ተፋሰስ የለማ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችትን ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል የተፈጥሮ ጋዝ የንግድ ስምምነት ተፈራረመ።

በኦጋዴን አካባቢ 8 ትሪሊየን ጫማ የሚገመት የተፈጥሮ ጋዝና መጠኑ እየተለየ ያለ ፈሳሽ ነዳጅ በመገኘቱ ወደ ልማት እንዲገባ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በዚህም በአካባቢው የሚገኙትን ካሉብ እና ሂላላ እንዲሁም ሽላቦ የተባሉ የተፈጥሮ ጋዝ መስኮችን ለማልማት ፖሊ ጂ ሲ ኤል ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት ከተባለው የቻይና ኩባንያ ጋር የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርሟል።

ስምምነቱ የተፈጥሮ ጋዝ ልማቱ በተካሄደባቸው የካሉብና ሂላላ እንዲሁም ሽላቦ የተፈጥሮ ጋዝ መስኮች ላይ የለማውን ክምችት በቧንቧ መስመር በማስተላለፍ ለሃገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ነው።

በዚህም በቀን 190 ሚሊየን ኪዮብ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ በሃገር ውስጥ ለሚገነባ የማዳበሪያ ፋብሪካና ለሌሎች የሃገር ውስጥ ፍላጎቶች እየታየ አቅርቦቱ እንደሚወሰን ተገልጿል።

ወደ ውጭ የሚላከው የተፈጥሮ ጋዝ በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በሚዘረጋው የቧንቧ መስመር ጅቡቲ ወደብ ላይ በሚገነባው ወደ ፈሳሽ መቀየሪያ የተፈጥሮ ጋዝ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የሚቀርብ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ይህም በቀን 215 ሚሊየን ኪዩቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ፈሳሽ ጋዝ በመቀየር በዓመት 1 ነጥብ 5 ሜትሪክ ቶን ፈሳሽ ጋዝ ማቅረብ ያስችላል ተብሏል።

በዚህ ፕሮጀክት ሌሎች ግኝቶችን ሳይጨምር በሚቀጥሉት 20 ዓመታት 6 ቢሊየን ዶላር ማግኘት እንደሚያስችል በጥናት መረጋገጡንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.