Fana: At a Speed of Life!

በ2016 የመጻሕፍት ሥርጭትንና ቁጥጥርን ለማቀላጠፍ የዲጂታል መተግበሪያ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 ዓ.ም ሁሉንም የሀገሪቷን ትምህርት ቤቶች መሠረት በማድረግ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመጻሕፍት ሥርጭትንና ቁጥጥርን ለማቀላጠፍ የሚረዳ የዲጂታል መተገበሪያ ተግባራዊ ሊደረግ ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የመጻሕፍት ሥርጭትና ቁጥጥርን ለማቀላጠፍ የሚረዳ ‘ትራክ ኤንድ ትሬስ’ የተሰኘ ዲጂታል መተገበሪያ ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል፡፡

ዲጂታል መተግበሪያው በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አምስት ትምህርት ቤቶችን መሠረት በማድረግ ወደ ሙከራ ትግበራ መግባቱን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

መተግበሪያው ለተማሪዎች የመማሪያ መጻሕፍት አስተዳደር የሚያግዝ መሆኑ  ተገልጿል።

የዲጂታል መተግበሪያው የአገልግሎት ሽፋን ከመጻሕፍት አታሚ ድርጅቶች አንስቶ በተማሪዎች እጅ እስከሚደርስ ያለውን ሂደት እና የመጻሕፍት አገልግሎት ጊዜን ጭምር የሚያጠቃልል መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የሚታተሙ የተማሪ መማሪያ መጻሕፍት እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ‘ባርኮድና ኪውአር’ ያላቸው ሆነው እንደሚታተሙም ነው የተገለጸው፡፡

ከዚህ በፊት መጻሕፍት ከተማሪዎች እጅ እስከሚደርሱ ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ለብክነት ሲዳረጉ መቆየታቸው ተጠቁሟል፡፡

የዲጂታል መተግበሪያውም ይህንን ችግር ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.