25ኛው ዓለም አቀፍ የሐረር ቀን በቶሮንቶ እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የሐረሪ የባሕልና ስፖርት ፌስቲቫል አካል የሆነው 25ኛው ዓለም አቀፍ የሐረር ቀን በካናዳ ቶሮንቶ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡
በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ በካናዳ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ የሐረሪ ተወላጆችን ጨምሮ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
ከዓለም አቀፍ የሐረር ቀን ቀደም ብሎ በተካሄደው የሐረሪ የባሕልና ስፖርት ፌስቲቫል ላይ አቶ ኦርዲን በድሪ ባስተላለፉት መልዕክት ፌስቲቫሉ÷ ዳያስፖራው ከሀገሩ እና ከሕዝቡ ጋር ያለውን ትሥሥር እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ከዳያስፖራው ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረኮችን ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በካናዳ ቶሮንቶ ከሚገኘው ማኅብረሰብ ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነዋል፡፡