በባህር ዳር ከተማ በ650 ሚሊየን ብር የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት አገልግሎት ጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህር ዳር ከተማ በ650 ሚሊየን ብር የተገነባው የመጠጥ የውኃ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ሮጀክቱ በጃፓን መንግሥት ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ድጋፍና በክልሉ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ አሰሪነት ኮኖኬ በተሰኘው የጃፓን ተቋራጭ የተገነባ መሆኑን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታውቋል።
የውኃ ፕሮጀክቱ ከዘጠኝ ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች ንጹህ የመጠጥ ውኃ በማውጣት በተዘረጋለት የ42 ኪሎ ሜትር የቧንቧ መስመር ለ147 ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎች ተደራሽ የሚያደርግ ነው ተብሏል።
በአፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የተገነባው ይህ ፕሮጀክት አምስት ሚሊየን ሊትር ውኃ የመያዝ አቅም ያላቸው የውኃ ጋኖች የተገነቡለት ሲሆን፥ በሰከንድ 350 ሊትር ውኃ ለተጠቃሚዎች የማቅረብ አቅም እንዳለውም መረጃው አመላክቷል።
እንዲሁም ውኃን ከተለያዩ ጉድጓዶች ተቀብለው ወደ እነዚህ ጋኖች የሚልኩ ባለ አንድ ሚሊየን ሊትር፣ ባለ 700 ሺህ ሊትር እና ባለ 200 ሺህ ሊትር የማቀባበያና የውኃ ማከሚያ ጋኖች እንደተገነቡለት ተጠቅሷል።