ከ454 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አማካኝነት ከ454 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በተጨማሪም የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 11 ግለሰቦችና 4 ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል፡፡
ኮሚሽኑ ከሐምሌ 14 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል÷ 194 ሚሊየን የገቢ እና ከ260 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን ገልጿል፡፡
ከተያዙት ዕቃዎች መካከል÷ አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ መያዛቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡