በ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የካዛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታና የተንዳሆ ፒ.ሲ. 16 መልሶ ግንባታና ጥገና ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመስኖ ልማት ኮሚሽን ከሶስት የስራ ተቌራጮች ጋር በ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የካዛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታና የተንዳሆ ፒ.ሲ. 16 መልሶ ግንባታና ጥገና ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ኮሚሽኑ ስምምነቱን የተፈራረው ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ፣ከሱር ኮንስትራክሽን ፕ.ኤል.ሲ. እና ከአፋር ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ጋር ነው።
ስምምነቱ የካዛ ግድብ ግንባታና ተያያዥ ስራዎች ሎት አንድ ፣የካዛ መስኖ ልማትና ዲሬይኔጅ ስራዎች ሎት ሁለት እና የተንዳሆ ፒ.ሲ. 16 የመልሶ ግንባታና የጎርፍ መከላከያ ዳይክ ጥገና ፕሮጀክቶችን ለማከናወን የሚያስችል መሆኑን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በዚሁም መሰረት የካዛ ግድብ ግንባታና ተያያዥ ስራዎች ፕሮጀክትን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ፣ የካዛ መስኖ ልማትና ዲሬይኔጅ ስራዎች ፕሮጀክትን የሱር ኮንስትራክሽን ፕ.ኤል.ሲ. በ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብርና የተንዳሆ ፒ.ሲ. 16 የመልሶ ግንባታና የጎርፍ መከላከያ ዳይክ ጥገና ፕሮጀክትን የአፋር ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በ433 ሚሊየን ብር ወጪ እንደሚሰሩ ነው የተገለፀው።
የካዛ ግድብና መስኖ ልማት ሎት አንድና ሁለት በአራት ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን የተንዳሆ ፒ.ሲ. 16 የመልሶ ግንባታና የጎርፍ መከላከያ ዳይክ ጥገና ፕሮጀክት ደግሞ በአንድ ዓመት ከመንፈቅ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ታቅዷል።
በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የስራ ተቌራጮቹ የስራ ሃላፊዎች ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጿል፡፡
በተጨማሪም የፕሮጀክቶቹ ባለቤት የመስኖ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሚካኤል መሃሪ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ የስራ ተቌራጮቹ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው በመግለፅ በግንባታ ወቅት ከክልል ጀምሮ እስከ ታችኛው የመስተዳድር እርከን ድረስ በቅንጅት የሚያጋጥሙትበትን ችግሮች በጋራ ለመፍታት ይሰራል ብሏል ፡፡
የካዛ ግድብና መስኖ ልማት ሎት አንድና ሁለት 10 ሺህ ሄክታር የማልማት አቅም ያለውና ከ20 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የግድቡ ከፍታ 57 ሜትር እና ርዝመቱ ደግሞ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ነው፡፡