በክልሉ 272 ሺህ 994 ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተያዘው የመኸር ወቅት 272 ሺህ 994 ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር ዝግጁ እንደሆነ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ እና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፈ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ በክልሉ የመኸር እርሻ ስራ በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የዝናብ መቆራረጥ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ግን የዝናብ ስርጭቱ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ጥሩ እንደሆነ እና አርሶ አደሩም ማሳውን እያዘጋጀና ዘር እየዘራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
እንደ ክልል በመኸር ወቅት 323 ሺህ 294 ሄክታር መሬት በላይ ሰብል ለማልማት መታቀዱን ጠቅሰው፤ ከዚህም 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ለማልማት ከታቀደው ውስጥ 28 ሺህ 600 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር ለመሸፈን እና 1 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን ድረስ 272 ሺህ 994 ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን የገለጹት አቶ አሸናፊ፤ ለባለሙዎች ስልጠና ተሰጥቶ ለአርሶአደሩ በቂ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
80 በመቶ የሚሆነው መሬት መታረሱን እና 61 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት፡፡
በመኸር ወቅት የታለመውን መሬት በማልማት ሂደት ውስጥ የአፈር ማዳበሪ እጥረት ዋነኛ ችግር መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በፌቨን ቢሻው