ዩኒቨርሲቲው ከአዘርባጃን አምባሳደር ጋር በጋራ ሊያሰሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያየ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የአዘርባጃን አምባሳደር ሩስላን ናሲቦቭ ከኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር በጋራ ሊያሰሯቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበሩ ታሪካዊ ግንኙነቶች በተለይም በዲፕሎማሲያዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በባህላዊ እንዲሁም በትምህርት ዘርፍ የነበራቸው ግንኙነት የቀደመና ታሪካዊ እንደሆነ ለአምባሳደሩ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከምስረታው ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ሙያተኞችን በማፍራት ለሃገር ያበረከተው አስተዋጽኦ ሰፋ ያለ እንደሆነና አሁንም የመከላከያን አቅም በመገንባት ወታደር ሙያተኞችን በማፍራት የተቋሙን ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ ያለ ግዙፍ ተቋም መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ ቀጣይ ከኤምባሲው ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር መግባባት ላይ በተደረሰባቸው ነጥቦች ላይ በማተኮር ውጤታማ ሥራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።
በጋራ ሊያሰሩ በሚቻልባቸው የትምህርትና የምርምር እንዲሁም የማማከርና የማኅበረሰብ ተኮር አገልግሎቶች ላይ ከቡድኑ ጋር ምክክር መደረጉን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል።
በዚህም በጋራ ሊሰሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የትብብር ማዕቀፍ እንዲኖር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በመከላከያ የውጭ ግንኙነት ደይሬክቶሬት በኩል ለአዘርባጃን ኤምባሲ እንዲቀርብ የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ከውይይቱ በኋላም አምባሳደሩና ልዑካቸው የኢነጂነሪንግ ኮሌጅ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ፣ አሌክትሮኒክስ ኢንጂነሪንግ ቤተ ሙከራዎች እና የኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ ሰርቶ ማሳያን ጎብኝተዋል።