ክልሉ በ560 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቡና በማልማት ከ40 ሺህ ቶን በላይ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ አቅርቧል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ2015 በጀት ዓመት በ560 ሺህ 20 ሄክታር መሬት ላይ ቡና በማልማት 42 ሺህ 611 ነጥብ 96 ቶን ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መላኩን ገለጸ።
የክልሉ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን እንዳስታወቀው፤ ባለፈው በጀት ዓመት 46 ሺህ 409 ያልታጠበ እና 18 ሺህ 187 ነጥብ 4 የታጠበ በድምሩ 64 ሺህ 596 ነጥብ 4 ቶን የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ ወደ ስራ ገብቶ ነበር።
በዚህም 29 ሺህ 573 ነጥብ 80 ያልታጠበ፤ 13 ሺህ 38 ነጥብ 162 የታጠበ በድምሩ 42 ሺህ 611 ነጥብ 96 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የእቅዱን 65 ነጥብ 68 ብቻ ማሳካት እንደተቻለ ገልጿል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የቡና፣ ሻይና ቅመማቅማም ልማትና ጥበቃ ዘርፍ ኅላፊ አቶ በላይ ኮጁአብ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት አፈጻጸሙ ቀደም ካለው በጀት ዓመት አንጻር ቀንሷል።
የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ መዋዠቅ፣ በግለሰብ ቤት ቡና ተከማችቶ መቀመጥና የቡና የምርመራ ሰርተፍኬሽን ማዕከል መራቅ ለአፈጻጸሙ መቀነስ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት በ585 ሺህ 19 ሄክታር መሬት ላይ ቡና በማልማት 67 ሺህ 340 ቶን ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን አመላክተዋል፡፡
ለዚህም በስፋት ቡና ከሚያመርቱ ዞኖች በተጨማሪ በተቀሩት የክልሉ አካባቢዎች የቡና ተክልን ለማስፋፋት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 7 ሺህ 16 ቶን ሻይቅጠል ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ 6 ሺህ 164 ቶን በማቅረብ የእቅዱን 87 በመቶ ማሳክት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ክልሉ በሻይ ቅጠል አምራችነት ከሚታወቁ አካባቢዎች ውስጥ በግንባር ቀደምነት እንደሚጠቀስ አንስተዋል።
በፌቨን ቢሻው