Fana: At a Speed of Life!

ከ19 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የተባሉ ሁለት የባንክ ሰራተኞች ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሙስና ወንጀል ከ19 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በተባሉ ሁለት የባንክ ሰራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡

ተከሳሾቹ ክሱ የተመሰረተባቸው በ2007 ዓ.ም የወጣውን የሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 881/07 አንቀፅ 31/2/ እና የወንጀል ህግ 32/1/ (ሀ) ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ በፈፀሙት ወንጀል ነው።

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ከ19 ሚሊየን ብር በላይ የሙስና ወንጀልና ከባድ እምነት ማጉደል ወንጀል ፈጽመዋል ባላቸው ብርሃኑ ሀይሉ እና አብዱራዛቅ ኢሳቅ በተባሉ የብርሀን ባንክ አክሲዮን ማህበር በደሎ ኦዳ ቅርንጫፍ ሰራተኞች ላይ ክስ መሥርቷል።

1ኛ ተከሳሽ በብርሀን ባንክ አክሲዮን ማህበር በደሎ ኦዳ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ሆኖ በሚሰራበት ወቅት በባንኩ ተጥሎበት የነበረውን እምነት እና አደራ ወደ ጎን በመተው መጋቢት 16 እና ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም በጥቅሉ ከ18 ሚሊየን ብር በላይ በማጉደል ለግል ጥቅሙ ያዋለ በሚል ፈጽሞታል በተባለው ከባድ የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል ተከሷል።

ይኼው ግለሰብ በሁለተኛ ክስ ባንኩ ለሰራተኞች ብድር ሲሰጥ ተበዳሪው ፎርም ሞልቶ፣ ዋስ አቅርቦ ለተበደረው ብድር የሚመልስበት ጊዜ ተቀምጦለት ለተበደረው ገንዘብ በሰነድ ማረጋገጫ ሰጥቶ መሆን ሲገባው ተከሳሽ ይህንን ባለማድረግ ለቅርንጫፉ 11 ሰራተኞች 1 ሚሊየን 151 ሺህ 212 ብር ያለምንም የሰነድ ማስረጃና ቅድመ ሁኔታ የሰጠ መሆኑ ተጠቅሷ።

በተጨማሪም የባንኩ የደንበኞች መኮንን ሆኖ ሲያገለግል ከነበረው ሁለተኛ ተከሳሽ አብዱራዛቅ ይሳቅ ተከሳሾች አረጋግጠው መፈራረም ሲገባቸው ይህን ባለማድረግ ከካዝናው የ19 ሚሊየን 412 ሺህ 920 ብር ጉድለት እያለ በጥሬ ገንዘብ መመዝገቢያ መዝገብ ላይ ጉድለት እንደሌለ አረጋግጫለሁ በማለት 2ኛ ተከሳሽ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን የፈረመ በመሆኑ ተከሳሾች የሚሰሩበትን ሊጠብቁትና ሊከላከሉት የሚገባውን ህዝባዊ ድርጅት ጥቅም በከባዱ የሚጎዳ ተግባር የፈጸሙ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅትን ስራ በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ዐቃቤ ህግ አራት የሰው ምስክሮችንና ሦስት የሰነድ ማስረጃዎችን በማያያዝ ለፍርድ ቤት ማቅረቡን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

መዝገቡን የተመለከተው የድሬደዋ ፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሱ ከደረሳቸው በኋላ 1ኛ ተከሳሽ የክስ መቃወሚያ አቅርቦ በመቃወሚያው ላይ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም የተቀጠረ ሲሆን ተከሳሾችም እስከዛው ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ታዟል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.