የአፍሪካ ህብረት ኒጀርን ከአባልነት ተሳትፎ አገደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ህብረት በፈረንጆቹ ሐምሌ 26 ቀን 2023 የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ ኒጀርን ከሁሉም እንቅስቃሴዎቹ እንዳትሳተፍ ማገዱን አስታወቀ፡፡
ህብረቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ÷ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች በምርጫ ስልጣን የያዙትን ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙምን ከእስር እንዲፈቱ እና ወደ ቤታቸው እንዲመልሱ ጥሪ አቅርቧል።
የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የፀጥታው ምክር ቤት÷ የምዕራብ አፍሪካ ህብረት (ኢኮዋስ) ለወታደራዊ ጣልቃገብነት ተጠባባቂ ሃይል ለማንቀሳቀስ ያሳለፈውን ውሳኔ መመልከቱንም ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እንደዚህ አይነት ሃይል ማሰማራት ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና የደህንነት አንድምታ እንዲገመግም ጠይቋል።
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ዲሞክራሲን ወደነበረበት ለመመለስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ካልተሳካ ወታደሮቹን ወደ ኒጀር ለመላክ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
የአፍሪካ ህብረት ሁሉም አባል ሀገራቱ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኒጀርን ወታደራዊ ኃይል ህጋዊ ሊያደርግ ከሚችል ማንኛውም እርምጃ እንዲቆጠቡ ጠይቋል፡፡
ከአፍሪካ ውጭ የትኛውም ተዋናይም ሆነ ሀገር የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበለውም በአጽንኦት አስታውቋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!