የአብሮነት እሴትን ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በሕዝቡ መካከል ያለውን የአብሮነትና የአንድነት እሴት ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ።
በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች እና ከተሞች ሕዝባዊ የሰላም ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በጉባዔው ላይ እንደገለጹት÷ የአመለካከትና የጽንፈኝነት ችግሮችን በማስወገድ የሕዝቡን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል፡፡
በክልሉ የተጀመሩ የጸጥታና የሕግ የበላይነትን የማስፈን ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል፡፡
ሕብረተሰቡም የሰላም እሴቶችን በማጎልበት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊወጣ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የክልሉ መንግስት ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡