በዚምባብዌ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኤመርሰን ምናንጋግዋ በድጋሚ አሸነፉ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዚምባብዌ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኤመርሰን ምናንጋግዋ ለሁለተኛ ዙር መመረጣቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ተጭበርብሯል በሚል ለሁለተኛ ዙር በተካሄደው ምርጫ ኤመርሰን ምናንጋግዋ 52 ነጥብ 6 በመቶ ድምጽ በማግኘት ነው በድጋሚ ያሸነፉት፡፡
የምናንጋግዋ ዋነኛ ተቀናቃኝ እና “የሲትዝንስ ኮአሊሽን ፎር ቼንጅ” ፓርቲ መሪ ኔልሰን ቻሚሳ ደግሞ 44 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድጋሚ የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድቅ እንዳደረጉት አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በምርጫው የተሳተፉት ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችም በምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ላይ ጥያቄ ማንሳታቸው ተነግሯል፡፡
ኤመርሰን ምናንጋግዋ በፈረንጆቹ 2017 በቀድሞ የሀገሪቱ መሪ ሮበርት ሙጋቤ ላይ በተደረገ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ነበር ወደ ስልጣን የመጡት፡፡
ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን ሲመጡም ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግራሉ በሚል ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር፡፡
በአንጻሩ ዚምባብዌ በምናንጋግዋ ስልጣን ዘመን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ በዘገባው ተመላክቷል፡፡