ከ272 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ272 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 14 ግለሰቦች እና ስምንት ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የተመለከተው፡፡
ኮሚሽኑ ከነሐሴ 12 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል ነው የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አማካኝነት የተያዙት፡፡
የተያዙትም 151 ነጥብ 9 ሚሊየን የገቢ እና 120 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የወጭ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ከተያዙት ዕቃዎች መካከል÷ አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ መያዛቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡