ሁላችንም የጋራ ጠላት ተጋፍጠናል፤ ለየግል በሚደረግ ትግል ቫይረሱን ማሸነፍ አይቻልም- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትብብር እንጂ በግል በሚደረግ ትግል የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ -19) ማሸነፍ እንደማይቻል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ ትብብርን በማስመልከት ባቀረበው ጥሪ በማስመልከት ድጋፋቸውን በመግለፅ መልእክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በመልእክታቸው፥ ኮቪድ- 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ባስከተለው ጫና ምክንያት የሰዎች ማህበራዊ እና ኦኮኖሚያዊ መሰረቶች መናጋታቸውን እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን አንስተዋል።
በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ የዓለም ህዝቦች ለስራ አጥነት መጋለጣቸውን እንዲሁም በኢኮኖሚው ዘርፍም ዓለማችን በትሪሊየን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ማጣቷንም ጠቅሰዋል።
በተለይም ወረርሽኙ ተጋላጭ የሆኑ በአፍሪካ ባሉ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች ላይ ደግሞ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩን አንስተዋል።
በዓለም ላይ ቀውሶች ሲከሰቱ ሰዎች ራሳቸውን፣ የሚወዷቸውን ሰዎች እና ዘመዶቻቸውን ይዘው ይሸሻሉ ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ አሁን ያጋጠመው ቀውስ ግን የተለየ ነው፤ ሁላችንም ድንገት በአንድ ጀልባ ላይ ራሳችንን አገኘን ሲሉም ገልፀዋል።
እንዲህ አይነት ችግርን ማለፍ የሚቻለው በጋራ በመሆን ነው ያሉት ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ የትብብር ጥሪዎችም ለእርዳታ እንዳንሆን ግልፅ ሊሆን ይገባልም ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አክለውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ ያቀረቡትን የትብብር ጥሪ እደግፋለው በማለት፤ ከዚህ ውጪ ምንም አይነት አማራጭ እንደሌለም ገልፀዋል።
አሁን ባለው ዓለም አቀፍ ወረርሽ ወቅት በተግባር መዘግየት ማለት ሞት ነው፤ ሁላችንም ተመሳሳይ ጠላት ነው የተጋፈጥነው፤ ለየግል በሚደረግ ትግል ቫይረሱን ማሸነፍ አይቻልም፤ የኢኮኖሚያችን አቅም ቢለያይም ሁላችንም የሚጠበቅብንን ማበርከት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ኮቪድ- 19 ማንንም የማይለይ፤ ዓለም ሁሉ የሚያጠቃ ነው፤ በዚህ ውቅት በጣም ታጋላጭ የሆኑ በተለይም ሴቶች፣ ህፃናት እና የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎችን በተለየ መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
ሁሉም ሀይል በትብብር በመሆን ለኮቪድ -19 ወረርሽኝ ክትባት ፍለጋ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረቡት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።