ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ለአንድ ወገን ባደሉ ስምምነቶች ከልማት አትታቀብም -አምባሳደር መለስ ዓለም
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዳሴ ግድብ የቀጣናው እና የተፋሰሱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ፡፡
አምባሳደር መለስ ዓለም ÷ግድቡ ኢትዮጵያውያን ብዙ ሆነው እንደ አንድ በአንጡራ ሃብታቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው እየገነቡት የሚገኝ የኃይል ማመንጫ መሆኑንም አንስተዋል።
ግድቡ የትውልድን የዘመናት የልማት ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ጠቁመው÷ የግድቡ 4ኛ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅም ለኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት ገጸበረከት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በግድቡ ምክንያት ብዙ ተፅዕኖ ማስተናገዷን በማንሳት፤ በመርህ፣ በቁርጠኝነት እና በጥረቷ ፈተናዎችን ማለፍ ችላለች ያሉት፡፡
ግድቡ በኢትዮጵያውያን የውስጥ አቅም በሉዓላዊ ግዛታቸው ውስጥ የሚገነባ ቢሆንም ጥቅሙ ከሀገር ያለፈ ነው ብለዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኃይል ዘርፍ የጀመረችውን ትስስርና የኢኮኖሚያዊ ውህደት ጉዞ በእጅጉ የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የታችኛው የተፋሰስ ሀገራት የሚገኙ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንዳያጋጥማቸው እንዲሁም በቂ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ በማድረግም ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ግድቡ የቀጣናውንና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ፕሮጀክት መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
ከዚህ አኳያ ግድቡ የትብብር እንጂ የግጭት ምንጭ መሆን የለበትም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
4ኛው የውሃ ሙሌት የተከናወነው የፖሊሲ ነጻነታችንን መሰረት በማድረግና የኤሌክትሪክ ኃይል ያላገኙ 65 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን የሃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን አንዳንድ አካላት ጉዳዩን በተቃራኒው መውሰዳቸው የተሳሳተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ለሚደረግ ዘመቻ ምላሽና የሕዝብ ግንኙነት ስራ ውስጥ መግባት እንደማይፈልግም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም የተፈራረመችው ስምምነት እንደሌለ ገልጸው÷ ከዚህ አኳያ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙና ለአንድ ወገን ባደሉ ስምምነቶች ከልማት አትታቀብም ብለዋል።
ኢትዮያውያን የግድቡን ግንባታ እንዳገባደዱት ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ከኢትዮጵያ አልፎ የቀጣናው ብርሃን እንዲሆን ያደርጋሉም ነው ያሉት።
ከታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ጋር ከህዳሴ ግድብ ያለፈ ግንኙነት አለን ያሉት ቃል አቀባዩ ÷ኢትዮጵያ በልማት ትብብሮች፣ በህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ጉዳዮች በሚመለከት በትብብረ መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡