Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የሳተላይት ማዕከል መገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሳተላይት ማዕከል መገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተፈራርመውታል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሐም በላይ ማዕከሉ የሳተላይት አካላትን ለማምረት፣ ለመገጣጠምና ሙከራ ለማድረግ የሚያስችልና ንድፈ ሐሳብን ከተግባር በማቀናጀት የተጨበጠ ልምድና አቅም የሚገኝበት ልዩ ሃገራዊ መሠረተ ልማት መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም ባለፈው በቻይና እገዛ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳተላይት ማምጠቅ መቻሉን አስታውሰው፥ የዚህ ማዕከል መገንባት በራስ አቅም መስራት የሚቻልበትን እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ከዚህ አንጻርም ማዕከሉ በጋራ አመራር እውን ይሆናልም ነው ያሉት።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የጋራ ድጋፍ እንደሚተገበር አስረድተዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያደርጓቸው የነበሩ የንድፈ ሐሳብ ምርምሮች ወደ ተግባር የሚለወጡበት አሰራር እንዳልነበረ አውስተው፥ ማዕከሉ በዘርፉ የጋራ ምርምር ለማድረግ፣ ተጨባጭ ትምህርትና ልምድ ለማግኘትና ምርምሮችን ለሃገር እድገት ለማዋል ተባብሮ ለመስራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ማዕከሉ የሚገነባው ከአውሮፓ ሕብረትና ከፈረንሳይ መንግስት በተገኘ ድጋፍ እና በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር በዩኒቨርሲቲው በተዘጋጀ ቦታ ላይ ነው ተብሏል።

ግንባታው 50 ሚሊየን ዩሮ እንደሚፈጅ የተገመተ ሲሆን በ2013 በጀት ዓመት ይጀመራል መባሉን ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.