Fana: At a Speed of Life!

ብዙ መሪ ሀሳቦች ቢነገሩም የአፍሪካውያን ችግር ግን አልተቀየረም – ፕሬዚዳንት ቲኑቡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በየጊዜው ብዙ መሪ ሀሳቦች ቢነገሩም የአፍሪካውያን ችግር ግን እንዳለ ነው ሲሉ የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ ተናገሩ፡፡

በ78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ንግግር ያደረጉት የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቲኑቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለአፍሪካውያን እንቅፋት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የተገቡ ቃሎች አለመፈጸም፣ ኢ ፍትሃዊ አያያዝ እና ከውጪ የሚደረጉ ግልጽ ብዝበዛዎች በአፍሪካ እድገት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት መንግስታት ሀገራቸውን እንደገና ለመገንባት አዲስ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ማዋለዳቸውን በንግግራቸው አንስተዋል።

አያይዘውም በዚህ ሂደት የመጣው ይህ ታላቅ አካል የሆነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰው ልጅ ምኞቶች እና ምርጥ ሀሳቦች ምልክት እና ጠባቂ ሆኖ መመስረቱን አስረድተዋል።

ሀገራት ሌሎች ከፍርስራሽ እና ከጦርነት እንዲላቀቁ መርዳት ለራሳቸው ጥቅም እንደሆነ አይተዋል ያሉት ቲኑቡ÷ አስተማማኝ እና ግልፅ የሆነ እርዳታ በጦርነት የተዳከሙ ሀገራት ወደ ጠንካራ እና አምራች ማህበረሰብነት እንዲያድጉ አስችሏቸዋል ብለዋል።

አፍሪካ ለበርካታ አስርት አመታት ዋናውን ዕቅድ የሚገልፀውን ተመሳሳይ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የሃብት ተጠቃሚነት ስትጠይቅ ቆይታለችም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ።

የዛሬይቱ አፍሪካ እየተጋፈጠች ያለው የኢኮኖሚ ተግዳሮት ምክንያቶች ከጦርነቱ በኋላ አውሮፓውያን ካስተናገዱት በጣም የተለዩ መሆናቸውን እንገነዘባለን ሲሉም ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንት ቲኑቡ “የምንፈልገው ለአጋርነት እኩል የሆነ ፅኑ ቁርጠኝነት ነው” ማለታቸውን ዴይሊ ናይጄሪያን ዘግቧል።

የ2030 አጀንዳ እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የተሻሻለ ዓለም አቀፍ ትብብር እንፈልጋለን ሲሉም አጽንዖት ሰጥተዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.