የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 26 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የታደሙበት የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል የገዳ ስርአቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም መከበሩን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡
አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ የሀገሪቱና ከጎረቤት ሀገራት የመጡ እንግዶች እና ቱሪስቶች የታደሙበት የ2016 ሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል በሰላም እና በልዩ ድምቀት መከበሩን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል፡፡
የበዓሉ በሰላም መከበር የሀገሪቱን መልካም ገፅታ ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ግብረ-ኃይሉ አስታውሶ ለበዓሉ በሠላም መከበር የድርሻቸውን ለተወጡ ሁሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ፣ የበዓሉ አስተባባሪዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት፣ የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የመጡ እንግዶችን በገዳ ስርዓት እሴቶች መሰረት በወንድማማችነትና በእህታማማችነት መንፈስ ማስተናገዳቸው ተመላክቷል፡፡
ከዚህ ባሻገር ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ለበዓሉ ሰላማዊነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከታቸው እንዲሁም መላው የፀጥታ አካላት ኃላፊነታቸውን በብቃት በመወጣታቸው በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንደተከበረ የፀጥታና ደህንነት የጋራ-ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡
መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም በቢሾፍቱ የሚከበረው የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓልም በተመሳሳይ ሁኔታ በሰላም እንዲከበር ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡