ከንቲባ አዳነች የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋና አቀረቡ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 26 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ዕሴቱን ጠብቆ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች የ2016ዓ.ም ሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ሚሊዮኖች በተገኙበት ዕሴቱን ጠብቆ በሰለም ተከብሮ ተጠናቋል ብለዋል።
ይህን አስመልክቶ ከንቲባ አዳነች በሰጡት መግለጫ÷ለበዓሉ በሰላም መጠናቀቅ የበኩላቸውን ለተወጡ አካላት በሙሉ እና ለታየው አብሮነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ኢሬቻን የሚያጎሉ ሁነቶች ጎልተው የታዩበት ደማቅ በዓል አዲስ አበባ አስተናግዳለች ያሉት ከንቲባዋ የመዲናዋ ነዋሪዎች ለእንግዶቻቸው ያላቸውን አካፍለው አስተናግደዋልም ነው ያሉት፡፡
አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ከተማ ናትና እንደ ባሕልና ወጋቸው ከኦሮሞ ወገኖቻችሁ ጋር በፍቅርና በወንድማማችነት መንፈስ በዓሉ ላይ ታድመው ከተማውን በማድመቅ ለቱሪዝም መዳረሻነት ያላትን አቅም አሳይተዋል ነው ያሉት፡፡
የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎችና ከተሞች የመጡ ኢትዮጵያውያን በባሕላዊ አልባሳትና ጨዋታዎቻቸው አዲስ አበባ ከተማን ማድመቃቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከንቲባዋ ዛሬ በኢሬቻ ላይ የታየው አንድነት፣ አብሮነት እና የወንድማማችነት መንፈስ በሌሎች ጉዳዮቻችን ላይ ሊደገሙ ይገባል ብለዋል።
በመራኦል ከድር