ባለፉት 3 ወራት ስኬታማ ሥራ መከናወኑን የጋራ ግብረ- ኃይሉ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሦስት ወራት ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራቱ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡
ግብረ-ኃይሉ ባለፉት ሦስት ወራት ያከናወናቸው ተግባራት፣ የተገኙ ስኬቶች እና ውስንነቶችን ዛሬ ገምግሟል፡፡
ግምገማውን ተከትሎም ግብረ – ኃይሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው÷ ሕዝባዊ፣ መንግስታዊ እና ሃይማኖታዊ ሁነቶች፣ የጳጉሜን ቀናት፣ የዘመን መለወጫ፣ የመስቀል፣ የመውሊድ እና የኢሬቻ በዓላት ሲከበሩ እንዲሁም የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ- ሥርዓት ሲካሄድ ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲጠናቀቁ በቅንጅት መሠራቱን ገልጿል፡፡
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ሙያዊ አቅሙን እየገነባ፣ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ትጥቆችን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ሕግን በተከተለ ሁኔታ ውጤታማ የፀጥታ ሥራ ማከናወኑም ነው የተመላከተው፡፡
በተከበሩ ሁነቶች ሁሉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ጋር በትብብር በመሥራታቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብሏል ግብረ-ኃይሉ በመግለጫው፡፡
በቀጣይ 100 ቀናት የሚከናወኑ ተግባራትን ለይቶ የኢትዮጵያን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እንደሚሠራም ገልጿል፡፡
ወደፊትም የሚከናወኑ ሀገራዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ተግባር ተጠብቀው÷ በሰላም እንዲከበሩ እንሠራለን ነው ያለው ግብረ- ኃይሉ፡፡
ግብረ-ኃይሉ ሥራዎቹን ተግባራዊ የሚያደርግበት ዕቅድ አዘጋጅቶ እስከታችኛው ፈፃሚ አካል ድረስ ያወርዳል ብሏል መግለጫው።
ሰላምና ፀጥታን የማስከበር ሥራ በተሳካ ሁኔታ እንዲተገበር የሕብረተሰቡ ተሳትፎ በተለመደው ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ግብረ-ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሕብረተሰቡን እስከ ታች ወርዶ በማወያየት ተሳትፎውን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር እና የፀጥታና የደኅንነት አካላትን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጫው አመላክቷል፡፡