የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሀገር የሳይበር አቅም ማሳያና ኩራት የሆነ ተቋም ነው – አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 4 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ቀድሞ በመለየት፣ በማክሸፍና በመቆጣጠር የሀገርን የሳይበር አቅም ማሳያና የሀገር ኩራት የሆነ ተቋም ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
አቶ ደመቀ በ4ኛው ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የመክፈቻ ፕሮግራም እና በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በቀረበው “ሥውር ውጊያ” የፊልም ምርቃት መርሐ ግብር ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡
በዚህ ወ ቅት ባስተላለፉት መልእክት÷ የሳይበር ምህዳር እንደ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ብዙም ባላደጉ ነገር ግን በጂኦ-ፖለቲካው መስክ በስውርና በግልጽ የሃገራትን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚረባረቡበት መስክ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን አያይዘው ኢትዮጵያ ከምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ብሄራዊ ጥቅሞችን ተጻራሪ ከሆኑ ሃይሎች በተደጋጋሚ የሳይበር ጥቃት እየተሰነዘረ መሆኑ ግልጽ ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ጫና ከሚያቃልሉ ጉዳዮች መካከል ጠንካራ የሳይበር መከላከልና ማምከኛ አቅም መፍጠር እጅግ በጣም ወሳኝ ዘርፍ እንደሆነ መናገራቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡