Fana: At a Speed of Life!

ሕግና ሥርዓትን በመከተል የአማራን ሕዝብ ጥያ ቄዎች ለመመለስ እየተሰራ ነው – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በመድረኩ በመከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ሌ/ጄ መሐመድ ተሰማ፣ በም/ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ደሳለኝ ጣሰውና የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) ተገኝተዋል።

አቶ አረጋ ከበደ ÷በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ወራት በተከሰቱ ግጭቶች አስተዋዩን የአማራ ሕዝብ ለከፋ ችግር የሚዳርጉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች መድረሳቸውን አንስተዋል።

የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ተለይተው ለተፈጻሚነታቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ባለበት ወቅት የሕዝብን ጥያቄ ሽፋን በማድረግ ክልሉን ለማተራመስ የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ሕዝባችን ላልተገባ ጉዳት ዳርገዋል ብለዋል።

ሕግና ሥርዓትን በመከተል የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በአማራ ክልል ምንም አይነት ችግሮች ቢኖሩ ተቀራርቦ በውይይት መፍታት እንጂ ራሳችንን ከሚያወድም ድርጊት መቆጠብ ይገባናል ነው ያሉት፡፡

ወደዚህ ግጭት የገቡትንም መምከርና ማረም ከመላው ሕዝብ እንደሚጠበቅ ጠቁመው÷ የችግሩ መፍትሔም መነጋገር እንደሆነ አጽንኦት መስጠታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

መንግሥት አሁን ላይ ያለውን ግጭት በማስቆም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከሚያከናውነው ተግባር ጎን ለጎን የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችና ያሉበትን የልማት ክፍተቶች ለመሙላት በቁርጠኝነት እየሠራ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል።

በተሳሳተ መረጃ በመደናገር ራሳቸውን ወደ ግጭት ያስገቡ ኀይሎች ሰላማዊ መንገድን እንዲከተሉ የተናገሩት ርዕሰ መሥተዳድሩ÷ መንግሥት ሁሌም ለሰላማዊ ውይይት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነም አስታውቀዋል።

በውይይት መድረኩ አሁን ላይ በደብረ ማርቆስና አካባቢው የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም መግባባት ላይ ተደርሷል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው÷የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት ተቀራርቦ በመነጋገር መሆኑንም አንስተዋል።

ሕዝብን ለችግር እያጋለጠ የሚገኘው የኑሮ ውድነት ግጭቶች ቆመው መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.