ሺ ጂንፒንግ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የግሪን ቤልት እና ሮድ አካል ሆኖ ሊደገፍ እንደሚችል አረጋገጡ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ከየልዑካን ቡድናቸው ጋር በመሆን በቻይና ታላቁ የሕዝብ አዳራሽ የሁለትዮሽ ውይይት አደረጉ፡፡
በውይይታቸውም÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የቻይና ኢንቨስትመንት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እመርታ የሚኖረውን አስተዋፅዖ አንስተዋል፡፡
አክለውም በተለይም በአምስቱ ቁልፍ ምሰሶዎች ማለትም÷ በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ አይሲቲ፣ ማእድን ልማት እና ቱሪዝም ላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲኖር የማበረታቻ ጥሪ አቅርበዋል::
ፕሬዚዳንት ሺ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀሏ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንኳን ደስ ያለዎት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነትም ከሁሉን አቀፍ ፅኑ ግንኙነት ወደ ሁኔታ የማይፈታው ስልታዊ ትብብር እና ወዳጅነት ደረጃ ከፍ ማለቱን በይፋ አብስረዋል::
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ- ግብርን ያደነቁት ፕሬዚዳንቱ÷ ከቻይናው አረንጓዴ ልማት ፖሊሲ ጋር ተናባቢ በመሆኑ የግሪን ቤልት እና ሮድ አካል ሆኖ ሊደገፍ እንደሚችል አረጋግጠዋል::