Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በእስራኤል ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በእስራኤል ወሳኝ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ገለጹ፡፡
ብሊንከን ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በቴል አቪቭ ሰዓታት የፈጀ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት ይፋ ያደረጉት፡፡
የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት እስራኤል በሃማስ ተዋጊዎች ላይ ከፍ ያለ ጥቃት ለማድረስ በዝግጅት ላይ ባለችበት ወቅት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የባይደን ጉብኝት የመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ ዋና አጋር ለሆነችው እስራኤል ወዳጃዊ ድጋፍን ያሳያል ተብሏል።
ባይደን የአሜሪካ ቁልፍ አጋር ወደሆነችው ዮርዳኖስ በማቅናትም ባለአራት-ወገን ጉባኤ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
በአማን በሚኖራቸው ቆይታም ከእስራኤል ጋር ሰላም ለመፍጠር የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የአረብ ሀገራት መሪዎች፤ የዮርዳኖሱን ንጉስ አብዱላህ 2ኛ እና የግብፁን ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል-ሲሲን እንደሚያገኙ ተመላክቷል፡፡
እንዲሁም ከፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጋር ይገናኛሉ መባሉን የአልጀዚራና የፍራንስ 24 ዘገባዎች አመላክተዋል።
በእስራኤልና በሀማስ መካከል በተፈጠረው ግጭት እስከ አሁን በእስራኤል በኩል የሟቾች ቁጥር 1 ሺህ 400 ደርሷል።
እስራኤል በሐማስ በሚመራው ጋዛ ላይ እገዳን በማጥበቅ ነዳጅ እንዳይገባ በመገደብ እና አካባቢውን በአየር በመደብደብ ከ2 ሺህ 800 በላይ ፍልስጤማውያንን ለህልፈት የዳረገ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ያፈናቀለ የአፀፋ እርምጃ መውሰዷም ተመላክቷል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.