Fana: At a Speed of Life!

የፍትሕ ሚኒስቴርና አይኦኤም በጋራ መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መከሩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ ሚኒስቴር እና የዓለም ዓቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በሶስት አመቱ የፍትህ አካላት የትራንስፎርሜሽን እቅድ ዙሪያ በጋራ ለመስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) እና የአይኦኤም ኢትዮጵያ ተወካይ ሳራ ባሻ ለሦስት ዓመታት የሚዘልቀው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ እንዲሆን በትብብር በሚሰራበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡

ኤርሚያስ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት የአይኦኤም ልምድ እና አለም አቀፋዊ ተደራሽነት የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ዋና ዋና ጉዳዮችን በመተግበር ረገድ ጠቃሚ ሚና አለው የሚል ጽኑ እምነት እንደዳላቸው ገልፀዋል፡፡

ሳራ ባሻ በበኩላቸው÷ አይኦኤም የኢትዮጵያ የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግና የእቅዱን ዓላማ ለማሳካት ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ተቋማቱ ባካሄዱት ምክክር በአቅም ግንባታ ዙሪያ፣ በባለሙያ ማጥራት፣ የህግ ግንዛቤ ለፍትህ ባለድርሻ አካላትና ማህበረሰቡ በአዲስ እይታ ከመፍጠር አንጻር፣ ሀገር አቀፍ የወንጀል ዳታቤዝ ማደራጀት፣ ሀገራዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስትራቴጂ መቅረፅና መተግበር፣ የንቃተ ህሊና የህግ አገልግሎት ስርዓትን መንደፍና መተግበር፣ የፎረንሲክ ምርመራ በክልሎች ተደራሽ ማድረግ፣ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ውጤታማነት ማጠናከር እና ሌሎች ላይ ያተኮሩ ሀሳቦችን አንስተው ተወያይተዋል።

ተቋማቱ በቴክኒክ ቡድን ደረጃ የበለጠ ለመወያየት መስማማታቸውን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.