Fana: At a Speed of Life!

በቀን 18 ሺህ ካሬ ሜትር ሴራሚክ የሚያመርት ፋብሪካ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ ተገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀን 18 ሺህ ካሬ ሜትር ሴራሚክ ማምረት የሚችል ፋብሪካ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር)÷ ከግንባታ ማጠናቀቂያ ግብዓቶች ውስጥ ስትራቴጂክ ግብዓት የሆነውን ሴራሚክ በሀገር ውስጥ ለመተካት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም በቢሾፍቱ ከተማ 2 ቢሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው ሀገር በቀሉ ካም የሴራሚክ ፋብሪካ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ፋብሪካው ከ25 ዓመት በላይ ሴራሚክ እና የሴራሚክ ውጤቶችን ከውጪ በማስገባት ሲሸጥ እንደነበርም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በሀገር ውስጥ ያለውን እምቅ አቅም በመገንዝብ ምርቱን በሀገር ውስጥ ለማምረት ፋብሪካ መገንባቱን ገልጸው÷ የፋብሪካው ግንባታ ሲጠናቀቅ በቀን 18 ሺህ ካሬ ሜትር ሴራሚክ ማምረት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይ የተወሰኑ መሰረተ ልማቶችን የማሟላትና የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎች ካሟላ በኋላ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

መንግስት በዘርፉ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንዲመጡ ጥረት እያደረገ መሆኑን አንስተው፤ የኮንስትራክሽን ግብዓት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ሲስፋፉ ከውጪ የሚመጡ ምርቶች ላይ ያለውን የዘርፉ ጥገኝነት ችግር እየተቀረፈለት እንደሚሄድም አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ 40 በመቶ የሚሆነው አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ግብዓት በሀገር ውስጥ አቅም የሚሸፈን ሲሆን÷ በሚቀጥሉት 7 ዓመታት ውስጥ 80 በመቶውን በሀገር ውስጥ ለመሸፈን መታቀዱ ተመላክቷል ።

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.