የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ፡፡
ከ300 በላይ የቻይና ኩባንያዋችን ያሳተፈ የኢትዮ – ቻይና የኢንቨስትመንት ፎረም በሻንሀይ ተካሄዷል፡፡
ፎረሙ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲና በተባባሪ የሀገሪቷ ኩባንያዎች መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
በመርሐ-ግብሩ የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ፣ የማዕድን ሚኒስትር ኢ/ር ሐብታሙ ተገኝና የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ተገኝተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ትኩረት በምትሰጣቸው ዘርፎች ፣ያላትን ዕምቅ የማዕድን አቅም እና ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ ሁኔታ በሚመለከትም የሥራ ኃላፊዎቹ ገለጻ ማድረጋቸውን በቻይና ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በቀጣይ ከኤምባሲው ጋር በመተባበር ለቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝትና መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ለማፈሰስ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውም ተመላክቷል፡፡