ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የመከላከያ መረጃ ማዕከል መሰረተ ልማት ግንባታን መርቀው ስራ አስጀመሩ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የመከላከያ መረጃ ማዕከል መሰረተ ልማት ግንባታን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ሻለቃ አስፋው አናሞ መሠረተ ልማቱ የሰራዊቱን የወትሮ ዝግጁነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ግንባታውን ለማጠናቀቅ 1 አመት ከዘጠኝ ወራት እንደፈጀ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመርሐ ግብሩ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፣ የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ሀላፊ ሌተናል ጀነራል ደስታ አብቼ እንዲሁም ሌሎች የሰራዊቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ታድመዋል።
116ኛው የመከላከያ ሰራዊት ቀን ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ይሆናል።
በተጨማሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በቢሾፍቱ የሚገኘውን የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ የአየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከልን መርቀው ከፍተዋል።
በመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ የተገነባው የአየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከሉ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቢሮዎች፣ ሆስፒታልና ካፍቴሪያን አካቷል።
በዛሬው ዕለት የተመረቁት የመረጃ ማዕከልና የአየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል ለሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች የቁልፍ ርክክብ መደረጉ ተገልጿል፡፡