ከውስጥና ከውጭ የሚቃጣን ጥቃት በሩቁ የሚያስቀር ሠራዊት እየተገነባ ነው – ሌ/ጀ ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 11 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ላይ ከውስጥና ከውጭ የሚቃጣ ጥቃትን በሩቁ የሚያስቀር ሠራዊት እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ገለፁ።
116ኛው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተከብሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ የአየር ኃይሉ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።
ሌተናል ጀነራል ይልማ በዚህ ወቅት÷ሠራዊቱ በውስብስብና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ሁሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሟንና ሉዓላዊነቷን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስከበር መሆኑን ተናግረዋል።
የሠራዊት ቀን ሲከበር ህዝቡ ለሠራዊቱ እውቅና የሚሰጥበትና የሠራዊት አባላት ደግሞ ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ህይወታቸውን ለመስጠት ዳግም ቃል የሚገቡበት ነው ብለዋል።
በሁሉም አቅሞች የውጊያ ዝግጁነትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያ እንዳትደፈር የሚያስችል ጠንካራ ሠራዊት አየር ኃይልን ጨምሮ በሁሉም አውዶች እየተደራጀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይልን በዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ በቴክኖሎጂ፣ ብቃት ባለው የሰው ኃይልና በመሠረተ ልማት የማደራጀት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ የተገነቡ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችም በዛሬው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል፡፡