Fana: At a Speed of Life!

በትምህርት ቤት ምገባ አዲስ አበባ ልምድ የሚቀሰምባት ከተማ ሆና ተመረጠች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር አዲስ አበባ ሌሎች ሀገራት ልምድ የሚቀስሙባት ከተማ ሆና መመረጧን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በፓሪስ በተካሄደው የዓለም የትምህርት ቤት ምገባ ጥምረት መድረክ ላይ አዲስ አበባ ሌሎች ሀገራት ልምድ የሚወስዱባት ከተማ ሆና መመረጧን ገልጸዋል፡፡

እንደ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር ተጠቃሚ የሆኑ የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች ያሳዩት አበረታች ውጤት፣ በምግብ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ የሚቀር ተማሪ ቁጥር መቀነስ እና በምገባ መርሐ ግብሩ ለእናቶች የተፈጠረው የሥራ ዕድል በመድረኩ መነሳቱን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም መርሐ ግብሩን ከከተማ ግብርና ጋር ማጣመር በመቻሉ እና የምገባ ማዕከል በማቋቋም በዘላቂነት በመምራት አዲስ አበባ ከተማ ላሳየችው ዓርአያ የሚሆን ተግባር ሌሎች ሀገራት ልምድ ሊወስዱባት እንደሚገባ ተመርጣለች ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም የምገባ መርሐ ግብሩ የትውልድ ግንባታ አካል በማድረግ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ከንቲባ አዳነች ያረጋገጡት፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.