የሌማት ትሩፋት የአርሶአደሩን ኑሮ ከማሻሻል ባሻገር ለወጣቶች የስራ እድል እየፈጠረ ይገኛል- ወ/ሮ ሚስራ አብደላ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሌማት ትሩፋት የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል በተጨማሪ ለወጣቶች የስራ እድል እየፈጠረ ይገኛል ሲሉ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሚስራ አብደላ ገለጹ፡፡
የሐረሪ ክልል ግብርና ቢሮ በሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ÷ የሌማት ትሩፋት የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ ለወጣቶችም የስራ እድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በትንሽ መሬት ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና ምርቶችን ማምረትና እንስሳትን ማርባት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
ጤናማና ብቁ የሆነ ትውልድን ለመፍጠር ስርዓተ ምግብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለዚህም የሌማት ትሩፋት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አመላክተዋል።
በመድረኩ ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የግብርና ባለሞያዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡
በምንያህል መለሰ