Fana: At a Speed of Life!

ለፈረንሳይ አምራች ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን በተመለከተ ገለጻ ተደረገ 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ላሳዩ ለፈረንሳይ አምራች ኩባንያዎችና ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በተመለከተ ገለጻ መደረጉ ተነገረ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ እና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን አማራጮቹ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ አክሊሉ ታደሰ÷ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው የኢንቨስትመንት ማዕከሎች በርካታ አዋጭና ምቹ አማራጮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና የንግድና የሎጂስቲክ ዘርፍ እንዲሁም በባሕርዳር እና ጂማ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ እምቅ እድሎች እንዳሉ አሳውቀዋል።

እንዲሁም በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአግሮ ፕሮሰሲግ ዘርፍ የተሰማራው ግዙፉ የፈረንሳይ የብቅል አምራች ኩባንያ ሱፍሌ ኢትዮጵያ በውጪ ምንዛሪ ታስገባው የነበረውን ምርት ሙሉ በሙሉ በማስቀረት በኩል ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ከ50 ሺ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር መፍጠሩን በማስታወስ ኮርፖሬሽኑ በፓርኮቹ በኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ፍላጎቱ ላላቸው አዳዲስ ኩባንያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በመድረኩ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን፣ የተገነቡና ለአምራቾች የቀረቡ አስቻይ መሰረተ ልማቶች ላይ ገለጻ መደረጉን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላታል፡፡

በተጨማሪም ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችንና ማበረታቻዎችን እንዲሁም መሰል ዝርዝር ኢንቨስትመንት ተኮር ጉዳዮችን የተመለከተ ዝርዝር ሰነድ ቀርቦ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል ተብሏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.