Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ቀንን በማስመልከት “የህንድ-አፍሪካ አጋርነት” በሚል መሪ ቃል የቪድዮ ኮንፈረንስ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካ ቀንን በማስመልከት “የህንድ-አፍሪካ አጋርነት እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት  ቀጣይ እርምጃዎች” በሚል ርዕስ የቪድዮ ኮንፈረንስ ተካሄደ።

በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ በቪዲዮ ኮንፈረንሱ ላይ የተሳተፉ ሲሆን፥ ቀኑን በማስመልከት ንግግርም አድርገዋል።

በቪዲዮ ኮንፍረንሱ  ላይ አምባሳደሮች፣ ከፍተኛ ኮሚሽነሮች፣ ከህንድ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ሀላፊዎች፣ ታዋቂ የህንድ እና የአፍሪካ ዲፕሎማቶች እንዲሁም ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

አምባሳደሯ የአፍሪካ ቀንን በዚህ መልኩ እንዲከበር ላስተባበሩ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ መንግስት የቫይረሱ ስርጭትን ለመቆጣጠር እየወሰደ ስላላቸው የተለያዩ እርምጃዎች አብራርተዋል።

ለአብነትም በከፍተኛ ሚኒስትሮች ደረጃ የሚመራ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ዝግጅት እና አስተባባሪ ግብረ ሀይል መቋቋሙን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ከዚያም ባለፈ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማገዝና ኢኮኖሚውን ለመጠበቅ ሰፊ የሆነ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።

አምባሳደር ትዝታ አያይዘውም የኢትዮጵያ መንግስት አፍሪካን በመወከል የቡድን 20 አባል ሀገራት ለአፍሪካ የእዳ ስረዛ፣ የእፎይታ እና የቫይረሱ ስርጭትን ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ ማእቀፍ እንዲያቀርቡ በመጠየቅ በአፍሪካ ወሳኝ ሚና  መጫወቱን  ገልጸዋል።

አምባሳደሯ በዚሁ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና በሀንድ አቻቸው መካከል በፈረንጆቹ  ግንቦት 6 ቀን 2020 የተደረገውን የቴሌኮንፎክስ ስብሰባ በማስታወስ የህንድ መንግስት ለኢትዮጵያ የህክምና  መሳሪያ አቅርቦትን በማድረጉ አመስግነዋል።

አያይዘውም የህንድ መንግስት ለኢትዮጵያ ብሎም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በርካታ ዘርፈ ብዙ እርዳታዎችን መስጠቱን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ከዚህ በፊት የተካሄዱትን ሶስት የህንድ-አፍሪካ የስብሰባ መድረክ ውጤታማ መሆናቸውን አስታውሰው፥ የአፍሪካ ህንድን ግንኙነትን የበለጠ ለማጎልበት የሚያደርጉ ትብብርሮች መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ከዚያም  ባለፈ ይህንን ወረርሽኝ ለመቅረፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመጨረሻም አምባሳደር ትዝታ የሕንድ ኢግዚም ባንክ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በግብርና ፣ በመድኃኒት ምርቶች እና በመረጃ ቴክኖሎጂዎች ላይ የተሰማሩ የህንድ ኩባንያዎች የኮቪድ -19ን መከላከያ መሳሪያዎችን ማቅረብ እንዲችሉ እንዲያግዝ እና የብድር ክፍያ እፎይታ እና ስረዛ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን በህንድ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.