በኢትዮጵያ የሀሳብ ልዩነት ጠላትነት አለመሆኑን ደጋግሞ ማሳሰብ አስፈላጊ ነው – ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሀሳብ ልዩነት ጠላትነት አለመሆኑን ደጋግሞ ማሳሰብ አስፈላጊ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቷ በሶማሊ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እየተከበረ በሚገኘው 18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ እንደ ሀገር ለመቀጠል ከሕብረ ብሔራዊ አንድነት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ብለዋል፡፡
የበዓሉ መከበር ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውን እርስ በርስ እንዲጋሩ እና እንዲያስተዋውቁ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡
ጥፋትና ጥቃትን ተባብረን ነው መዋጋት ያለብን ያሉት ፕሬዚዳንቷ÷ የምንወዳት ሀገራችንንና ታላላቅ ህዝቦቻችንን ከችግር ማውጣት አለብም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከችግር ማውጣት ብቻ አይደለም የሚጠበቅብን፣ ወደፊት ማደግና ህዝቦቻችን እንደሌላው ዓለም ሁሉ ሙሉ በሙሉ ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን እንዲገቡ ሁኔታውን ማመቻቸት አለብን ብለዋል።
ከልዩነት አንድነትን መከባበርና እኩልነት፣ ከግጭት ይልቅ መቻቻልና ለሐሳብ ልዕልና ቅድሚያ መስጠት አንድነታችንን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት እንደሚያስችልም አንስተዋል።
ጫፍ የረገጠ ብሔርተኝነት አሁን ላይ እየተስተዋለ ነው፤ ይህም ኢትዮጵያዊነትን እያሳነሰ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።
ግጭቶች ሲከሰቱም በውይይትና በአካታች ምክክር መፍታት ይገባል ሲሉም ፕሬዚዳንቷ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡