Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያና በብሪታኒያመካከል ያለውን የልማት ትብብር በይበልጥ ማሣደግ እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና በብሪታኒያ መካከል ያለውን የልማት ትብብር በይበልጥ ማሣደግ እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ አመላከቱ፡፡

አቶ አሕመድ ሺዴ ከብሪታኒያ የውጭ የጋራ ብልጽግናና ልማት ጽሕፈት ቤት ቋሚ ተጠሪ ኒክ ዳየር ጋር በሀገራቱ የልማት ትብብር ላይ ውጤታማ ውይይት አድርገዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት የረጅም ጊዜ አጋርነት አጠናክሮ በማስቀጠል ረገድ የብሪታኒያ መንግሥት በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መንገዶች እያደረገ ላለው የልማት ድጋፍ አቶ አሕመድ አመሥግነዋል፡፡

ብሪታኒያ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ አባል ለመሆን መወሰኗንም አድንቀዋል፡፡

የኢትዮጵያን ወቅታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ እና ሰብዓዊ ሁኔታ እንዲሁም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና ከዓለም ባንክ ጋር ስላላት ጠንካራ መልካም ግንኙነትም አብራርተዋል፡፡

በቀጣይም በኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ መካከል ያለውን የልማት ትብብር በይበልጥ ማሣደግ እንደሚገባም በአጽንኦት መግለጻቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ኒክ ዳየር በበኩላቸው÷ የብሪታኒያ መንግሥት የኢትዮጵያን የልማት ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

አሁንም በብሪታኒያ ዓለም አቀፍ የልማት ድጋፍ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ሀገር መሆኗንም ነው ያስታወቁት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.