የሲቪክ ማህበራት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ቁልፍ ሚና ለሚኖረው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሲቪክ ማሕበራት አስታወቁ።
ሀገራዊ ምክክሩ ሲንከባለሉ የቆዩ የግጭት መንስኤዎችና ልዩነቶች ላይ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር እና የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማሕበር ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንቶች÷ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለምክክሩ ውጤታማነት በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ፕሬዚዳንት ዩሐንስ በንቲ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ቁልፍ መፍትሄ ነው።
ምክክሩ የግጭት መንስኤ የሆኑ የሀሳብ ልዩነቶችን ወደ አንድ መድረክ አምጥቶ ለመወያየትና እልባት ለመስጠት እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት፡፡
በመሆኑም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያገባኛል የሚሉ አካላት በሰከነ መንገድ በመወያየትና የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።
ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ በመጠቀም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በማገዝ በኩል ማሕበሩ የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማሕበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው÷ ማህበሩ የምክክር ኮሚሽኑ ከተዋቀረ ጀምሮ የበኩሉን ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ የውይይት ተሳታፊዎች ልየታ ስራ ላይ መሳተፉን ጠቁመው÷ በዚህም በክልልና በፌዴራል ደረጃ በምክክሩ ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ አካላትን ለኮሚሽኑ ማሳወቁን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማልማትና የተጀመረውን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠልም የጋራ መግባባት መፍጠር ምትክ የማይገኝለትና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ለሀገራዊ ምክክሩ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ካሳሁን÷ በመደማመጥ፣ በመግባባትና የሃሳብ ልዩነቶችን አክብሮ ወደ መፍትሔ ለመምጣት ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።