አየር መንገዱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛ ትውልድ የአየር ቲኬትና የሆቴል መስተንግዶ ዋጋ ቅናሽ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛ ትውልድ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ለሚገቡ የዳያስፖራ አባላት የአውሮፕላን ትኬትና የሆቴል መስተንግዶ ዋጋ ቅናሽ ማድረጉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለጸ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ እንደገለጹት÷ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር ) በተለያዩ ጊዜያት ለዳያስፖራ አባላት ጥሪ ሲያቀርቡ አየር መንገዱም የበኩሉን ኃላፊነት ሲወጣ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛ ትውልድ አባላት ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ለሚገቡት የዳያስፖራ አባላት አየር መንገዱ ከ15 እስከ 20 በመቶ የአውሮፕላን ቲኬት ቅናሽ ማድረጉን ገልጸዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አካል በሆነው የስካይ ላይት ሆቴል ለሚያርፉ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በተመሳሳይ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽና ለእንግዶቹም ልዩ ዝግጀት ማደረጉን አብራርተዋል።