በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ትምህርት እንደሚጀምሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ከጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀምሩ የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል በተፈጠረው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በ2016 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያው ወሰነ-ትምህርት ተማሪዎቻቸውን ለመጥራትና መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸውን ሙሉ ለሙሉ መጀመር አልቻሉም ነበር።
ይህን ተከትሎም የትምህርት ሚኒስቴር ከክልሉ ኮማንድፖስት፣ የጸጥታ አደረጃጀቶችና የሚመለከታቸው አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ሲያካሂድ መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ፣ የአስሩ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልሉ ጸጥታ አካላት በጉዳዩ ዙሪያ መምከራቸው ተገልጿል፡
አሁን ላይም በክልሉ አንጻራዊ ሰላም የተፈጠረ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎችን መጥራትና ማስተማር እንደሚችሉ ውሳኔ ላይ መደረሱ ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም መሰረት ከፊታችን ከጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎችን ጠርተው የመማር ማስተማር ስራቸውን አንደሚጀምሩ መጠቀሱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ ተማሪዎችም ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚያደርጉትን ጥሪ እንዲከታተሉ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡