ኢትዮጵያ የፊታችን ሰኞ ብሪክስን በይፋ በአባልነት ትቀላቀላለች
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም በጆሃንስበርግ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባዔ ኢትዮጵያ የአምስት ሀገራት ጥምረት የሆነውን ማኅበር ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል፡፡
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ግብጽ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ኢራን በፈረንጆቹ ከ ጥር 1 ቀን 2024 ጀምሮ በይፋ የብሪክስ አባል እንደሚሆኑ ጥምረቱ አስታውቋል።
አምስቱ ሀገራት ጥምረቱን ሲቀላቀሉ የአባል ሀገራቱ ቁጥር ወደ 10 ከፍ ይላል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ለኢትዮጵያ ታላቅ ሁነትና መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሁሉን አካታች ለሆነና ለበለፀገ የዓለም ሥርዓት መስፈን ከሁሉም ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗንም ማረጋገጣቸው ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ለባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማደግና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሚናው የላቀ መሆኑን ደግሞ ምሁራን ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ በዓለም የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ተሰሚነቷና ተቀባይነቷ እንዲያድግ ብሪክስን መቀላቀሏ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው የሚያስረዱት፡፡
የብሪክስ ጥምረት ዓላማ የጋራ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማረጋገጥ መሆኑንን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህም የዓለምን ኢኮኖሚያዊና ፋይናንሳዊ አሠራሮችንና ንድፎችን ማሻሻል እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎችንና መመዘኛዎችን ማጠናከርና የተለያዩ ዘርፎችን ተደጋጋፊነት ማጠናከርን ያካትታል።
የጥምረቱ አባል ሀገራት ከዓለማችን ሕዝብ 40 በመቶ የሚገኝባቸው፣ 26 በመቶ የዓለምን የምርት ምጣኔ የሚሸፍኑ እና 50 በመቶ የሚጠጋ የዓለም ኢኮኖሚ እድገት ባለቤቶች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ጥምረቱ አዲስ አባል ሀገራቱን መጠመሩ በዓለም የዲፕሎማሲ፣ ንግድና ኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውን ተጽእኖ እንደሚያሳድግለት ተንታኞች ይገልጻሉ።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!