ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ማሥተማር ተግባር ቅድመ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ ጥር ወር ለሚጀምረው የመማር ማሥተማር ተግባር ቅድመ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን አስታውቋል።
የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ታረቀኝ ትንታጉ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው ጥር አንድና ሁለት ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅቷል።
በተማሪዎች አገልግሎት በኩል የክሊኒክ፣ የመኝታ ክፍል፣ የመዝናኛ እና የቤተ መጽሐፍ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የምግብ አገልግሎት ግብዓት ማግኘት ፈታኝ ቢሆንም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ለተማሪዎች የምግብ አገልግሎት በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው ባለፈው አመት በካምፓሱ ውጤታቸውን ያሻሻሉ 3 ሺህ 400 ተማሪዎች በዘንድሮው አመት የመግቢያ ውጤት ያመጡ 600 ተማሪዎች በጥቅሉ 4 ሺህ አዲስ ተማሪዎችን ይቀበላል ተብሏል፡፡
በዘንድሮው አመትም 3 ሺህ 600 የሪሜዲያል ተማሪዎች እንደሚማሩ ታረቀኝ ትንታጉ (ዶ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
በአለባቸው አባተ