“የምስራቅ አፍሪካ አርብቶአደሮች ኤክስፖ” በጥር ወር ይካሄዳል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “የምስራቅ አፍሪካ አርብቶአደሮች ኤክስፖ” ከጥር 17 እስከ ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የቆላማ አካባቢዎችን የልማት ፀጋዎች በመጠቀም የአርብቶ አደሩን እና ከፊል አርብቶአደሩን ህይወት ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ተቋሙ የዚሁ ተግባር አካል የሆነውን እና በየሁለት ዓመቱ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የሚያከብረውን የአርብቶአደሮች ቀን ከወትሮው በተለየ መልኩ አህጉራዊ ትስስርን በሚያጠናክር መልኩ ከጥር 17 እስከ 23 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ አስታውቋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢ/ር አይሻ መሃመድ “የምስራቅ አፍሪካ አርብቶአደሮች ኤክስፖ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በኤክስፖው የኢጋድ አባል ሀገራት እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
አህጉራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩና በአርብቶአደሩ ህይወት ላይ ያተኮሩ የፓናል ውይይቶች፣ የልምድ ልውውጦች፣ የአርብቶአደሮች የልማት ፀጋዎችና የባህል አውደ ርዕዮች፣ የቴክኖሎጂና ቢዝነስ ፈጠራዎች እንዲሁም ሌሎች መርሐ ግብሮች ይከናወኑበታል ብለዋል፡፡
በመራኦል ከድር