ብሄራዊ የተቀናጀ የውኃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራምን በሚመለከት ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሄራዊ የተቀናጀ የውኃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም እና በሌሎች የውኃ ሀብት አስተዳደርን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከክልሎች የውኃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊዎችና የውኃ ሀብት አስተዳደር የሥራ ሀላፊዎች ጋር ውይይት እተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር፣ ኢ/ር)÷የውኃ ሃብት አጠቃቀም በአግባቡ እንዲመራ የዘርፉ ተዋናዮች ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ባለፉት አመታት በተተገበረው የቆላ ስንዴ መስኖ ልማት የገጠሩ ህብረተሰብ የመስኖ ጥቅምን መረዳት መቻሉንና በዚህም በእያዳንዱ ወንዝ ላይ ሰዎች እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘላቂ የውኃ ሀብት አስተዳደር ተጠቃሚዎችን መቆጣጠርና ማስተዳደር በሁሉም ክልሎች ወጥነት ባለው አግባብ መተግበር እንዳለበትም ጠቅሰዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የውኃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ውሃን መጠቀም፣ ማልማት፣ መጠበቅና መቆጣጠር በሚቻልበትና በሌሎች ውሃ ነክ ሥራዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
መድረኩ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ እና ክልሎች እስካሁን ያከናወኑት ተግባር ላይም ውይይት እንደሚደረግ መገለጹን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡